Senamirmir Senamirmir Projects Senamirmir Interviews Senamirmir Downloads Senamirmir Links Senamirmir Navigation Bar
Table of Contents Table of Contents Getting Started Navigation Bar

Printable Page



መቅድም

ዌብ ገጾች የሚጻፉት በHTML (Hypertext Markup Language) ነው። የቃላቶች አደራደር፥ የዐረፍተ-ነገሮች አሰካክ፥ የቀለሞች አቀባብ፥ የምስሎች አቀማመጥና የመሳሰሉት በHTML ደንብ መሠረት መገለጽ አለባቸው። ለዚህ አብዩ ምክንያት፥ የዌብ ገጽ መቃኛዎች ይዘቶችን እንዴት ማሳየት ወይም ማስነበብ እንዳለባቸው መመሪያውን የሚያገኙት ከHTML ስለሆነ ነው።

በHTML ብዙ አይነት ገጾችን ማውጣት ይቻላል። ይሁን እንጂ HTML በፍጹም መሥራት የማይችላቸው ነገሮች አሉ። ከነዚህ መካከል አንዱ ሥዕሎችን (vector graphics) መሣል ነው። ለምሳሌ፥ HTML ክብ ሥዕል ወይም በሕብር ቀለም የተሞላ ክብ ለመሣል የሚያስችል መመሪያ የለውም። በውጭ ፕሮግራሞች የተሠሩ ምስሎችን ማሳየት ይችላል፤ ነገር ግን የተለያዩ ቅርጾች መሣል የሚያስችሉ መመሪያዎች የሉትም።

እንደዚህ አይነት ድክመቶችን ለማረም ከሚቀርቡት መፍትሔዎች መካከል አንዱ፥ ከHTML ጋር አብሮ የሚሠራ አዲስ ቴክኖሎጂ ማውጣት ነው። SVG (Scalable Vector Graphics) የዚህ ውጤት ነው። በSVG የተለያዩ ዓይነት ሥዕላዊ ቅርጾችን ማውጣት፥ ቀላማትን መቀባት፥ ካንድ ቅርጽ ልዩ ልዩ መልክ ማውጣት፥ ዓይን የሚማርኩ እንቅስቃሴዎችን መፍጠር እንዲሁም ሌሎች ተግባሮችን መፈጸም ይቻላል። SVG ያለ ምንም ችግር ከHTML ጋራ ተዋሀዶ ወይም ለብቻው መቆም ይችላል።

የዚህ ጥናት ዓላማ SVGን ላንባቢው ማስተዋወቅ ነው። ምንም እንኳን በዌብ ገጽ መቃኛዎች በኩል ባሁኑ ወቅት ለSVG ያለው ድጋፍ አነስተኛ ቢሆንም፥ ወደፊት መምጣቱ አይቀርም። ለምሳሌ የሟዚላ (mozilla.org) ድርጅት SVGን ለመደገፍ ውጥን አውጥቶ በሥራ ላይ ነው። ባሁኑ ጊዜ፥ SVGን ያቀፈ የዌብ ገጽ ለማንበብ የሚያስችሉ ፕሮግራሞች አሉ። ስለዚህ SVGን በሥራ ላይ ማዋል እንችላለን።

በዚህ ጥናት ውስጥ፥ በSVG ላይ የተመረኮዘ ዌብ ገጽ ለመገንባት ምን እንደሚጠይቅ፥ የግንባታው ሂደት፥ የሥዕል አቀራረጽ ዘይቤዎች፥ የቀለም አቀባብ ዘዴዎች፥ የትዕይንተ-ሥዕል (animation) መላዎችና፥ የመሳሰሉትን እንማራለን። ከቀላል ምሳሌዎች በመጀመር ወደ ጠለቅ ያሉት እናመራለን።

ይህ ጥናት ምንም እንኳን መግቢያዊ ቢሆንም፥ ለመረዳትና በሥራ ላይ ለማዋል፥ ቢያንስ የሚከተሉትን ቅድማዊ ልምዶች ይጠይቃል። አንባቢው እነዚህ ልምዶች ከሌሉት ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ የፈቀደውን መሞከሩ ክፋት የለውም።

  • ትንሽም ቢሆን፥ በHTML ዌብ ገጽ የመጻፍ ችሎታ፤
  • መለስተኛ የአልጀብራ ዕውቀት፤
  • በትንሹም ቢሆን የXML ግንዛቤ።



Table of Contents Table of Contents Getting Started Navigation Bar

contact@senamirmir.org
Copyright © 2002-2005 Senamirmir Project