ሥነ ምርምር ምዕላደ-ቃላት |
|
|
|
በሕዝባዊ ቁልፍ ምስጢር አደባበቅ፥ bähêzêbawi kulêfê mêsêttirê adäbabäkê (public key cryptography)፤
፟በሕዝባዊ ቁልፍ ምስጢር ጥበቃ፠ ላኪውና ተቀባዩ የራሳቸው የሆነ ሁለት ፥ ሁለት ቁልፍ ይኖራቸዋል።
አንደኛው ቁልፍ የድብቅ-ቁልፍ ይባላል። ተቀባዩና ላኪው እነዚህን ቁልፎች በምስጢር ይጠብቃሉ።
ሁለተኛው የቁልፍ አይነት ገሀድ-ቁልፍ ይባላል። ይህ ቁልፍ በግልጽ መቀመጥ ይችላል። መደበቅ
አይኖርበትም። ምስጢር መላክ የሚፈልገው ወገን ይጠቀመዋል።
ደንብ፥ dänêbê (standard)፤
በጋራ ስምምነት ወይም ተቀባይነትን ያገኘ ሕግ፥ አሠራር፥ አጠቃቀም፥ አቀራረብ፥ አሠያየም፥ አገነኛኘት፥ አለካክና የመሳሰለው። እንደ ዩኒኮድ ያለው የፊደል ቦታ አመዳደብ፥ እንደ ቲሲፒ/አይፒ (TCP/IP) ያለው የኢንተርንት መገናኛ መንገድ ድንብ ናቸው።
መልክአ-ፊደል፥ mälêkêa-fidälê (typeface)፤
የፊደል ቅርጽ፥ አቋቋም፥ አቀጣጠን ወይም አወፋፈር፥ አዝማሚያ፥ አጣጣል።
ከፕሮግራም መውጣት፥ käpêrogêramê-mäwêttatê (exiting program)፤
የኮምፕዩተር ፕሮግራምን ከሥራ ማቆም፥ ማስወጣት።
ጥቁም፥ ttêqumê (index)፤
ምርጥ ስሞችን፥ መጠሪያዎችን፥ አርስቶችን፥ ፍሬ ቃላትንና እንዲሁም ገጾቻቸውን የሚናገር በመጽሀፍ መጨረሻ ላይ ወዳቂ ክፍል።
ፋይል፥ faiêlê (file)፤
የተጠናቀረ ወይም የተደራጀ ድጅታዊ ይዘት። ማንኛውም ፋይል እነዚህን ጠባዮች ይጨምራል፦ ስም፥ ጊዜ፥ መጠንና አይነት።
ፕሮግራም ማስነሳት፥ pêrogêramê-masênäsatê (running program)፤
የኮምፕዩተር ፕሮግራም ለሥራ ማሰማራት።
ዴታ፥ deta (data)፤
ጥሬ መረጃ። እውን ነገር ወይም ድርጊት ስለሀገረሰብ፥ ስለቦታ፥ ስለተፈጥሮ። ስም፥ አድራሻ፥ ቀን፥ መጠንና ሌሎችን ይጠቀልላል።
ኢንፎርሜሽን፥ inêforêmeshênê (information)፤
ወደዘገባነት የተቀየረ ዴታ ወይም ጥሬ መረጃ።
ዩዝነት፥ yuzênätê (USENET)፤
በኢንተርነት የውይይት መድረኮች። ከ40,000 በላይ የውይይት መድረኮች አሉ ይባላል። መድረኮቹ ይፋና ለሕዝብ ክፍት ናቸው። ይዘታቸው የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ያንጸባርቃል። ኢንተርነት ወደ ሀገረሰቡ ከመስረጉ በፊት፥ ዩዝነት የራሱ የሆነ ጥብቅ ባህል ነበረው። ዕውቀት መከፋፈል፥ አስተሳሰብ መለዋወጥ አብይ ዓላማዎች ሲሆኑ ከሸቀጥና «ከይኸን ግዙኝ» ማስተወቂያ ንጹሕ ነበር።
ዌብ ገጽ ጉብኝት፥ webê gäšê gubêñêtê (browsing web page)፤
ዌብ ገጾችን ከፍቶ ማንበብ፥ መመልከት፥ መጠቀም።
ሆሂያት ኮድ፥ hohiyatê kodê (character code)፤
ለያንዳንዱ ሆሄ የሚሰጥ ልዩ የቁጥር ስያሜ፥ የቦታ አደላደል። ለምሳሌ፥ የኢትዮጵያ ፊደል በዩንኮድ ውስጥ ስለገባ፥ ለያንዳንዱ ሆሄ የተመደበ የዩንኮድ ቁጥር/ቦታ አለ።
ኩዪሪ፥ kuyiri (query)፤
ለዴታቤዝ ሲስተም የሚቀርብ ጥያቄ፤ የተለያዩ ዴታዎችን ለማውጣት። ኩዪሪ የራሱ የሆነ የጥያቄ አቀራረብ መዋቅርና ሕግ አለው። ሰፊ ተጠቃሚዎች ያሉት የኩዪሪ አይነት በስኴል (SQL) የተመሠረት ነው።
ኤለክትሮኒክ መልክት፥ eläkêtêronikê mälêkêtê (email)፤
በኮምፕዩተር መረብ ተላላፊ ደብዳቤ ወይም መልክት። በቅርጹ ድጅታዊ፤ ፈጣንና አስማማኝ። አመቺ እንዲሁም ርካሽ።
ምስል፥ mêsêlê (image)፤
ያንድን ነገር እይታ ወይም መልክ የሚያሳይ/የሚገልጽ ሥዕል፥ ፎቶ፥ እንዲሁም የግራፊክስ ፋይል። በጽሑፍ ውስጥ የሚገቡ ሥዕሎች፥ ሠንጠረዦችና የመሳሰሉት ምስል ተብለው ይጠቀሳሉ።
ትእምርት፥ têêmêrêtê (sign)፤
ምልክት፤ አርማ።
ትሩታይፕ፥ têrutayêpê (truetype)፤
ፎንት መግለጫ ቋንቋ። ሆሄ እንዴት መሳል እንዳለበት መመሪያ ለመጻፍ የሚያስችል። መመሪያው በትሩታይፕ ላይ የተመሠረተ ፎንት፥ መልኩ ሳይዛነፍ ማስተለቅ፥ ማሳነስ፥ ማዟዟር፥ ማቅለም ይቻላል። የዊንዶስ ኦፕሬቲንግ ሲስተምስ፥ ሆሄያትን ለማሳይትና ለማተም ትሩታይፕ ፎንት ይጠቀማል።
ቱልባር፥ tulêbarê (toolbar)፤
ከኮምፕዩተር ፕሮግራሞች መስኮት የአርስት መስመር ቀጥሎ የተላያዩ ሥዕላዊ መመሪያ በተኖችን የያዘው ክፍል።
አባሪ፥ abari (attachment)
ከኤለክትሮኒክ መልክት ጋር በተደባይነት የሚላክ ፋይል። አብዛኛውን ጊዜ በመልክት ተቀባዩ በኩል ያለው የኤልክትሮኒክ መልክት ፕሮግራም መረዳት የማይችለው የፋይል አይነት ነው። ፕሮግራሙ አባሪ ፋይል ሲደርሰው፥ ላንባቢው አባሪ ፋይል መኖሩን ያስታውቃል። አንባቢው ፋይሉን ወደ ዲሰክ መክተት ወይም በሌላ ፕሮግራም መክፈት ይችላል።
ተራ ማስየዝ፥ tära masêyazê (sort)፤
ነገሮችን በቅደም-ተከተል ማሰለፍ፥ ማስቀመጥ፥ መደርደርና ማጠራቀም። የሥም ዝርዝሮችን በፊደል ቅደም-ተከተል መጻፍ። ጉዳዮችን በቀን ቅደም-ተከተል ማስያዝ።
ተለላ መስመር፥ täläla mäsêmärê (base line)፤
በጽሑፍ እያንዳንዱ ፊደል የሚጣልበት መሥመር። ለምሳሌ ደብተሮች ለጽሑፍ ያመቹ ዘንድ እያንዳንዱ ገጻቸው በተለላ መስመር የተከፈለ ነው። ጸሐፊዎች መሥመሩን ተከትለው ፊደላትን ይጽፋሉ።
በተን፥ bätänê (button)፤
አራት ማዕዘን ወይም ክብ ቅርጽ ያለው ሥዕላዊ መመሪያ። በማውስ የምንረገጠው ወይም
ከመረጥን በኃላ በኢንተር ቁልፍ (
ቋሚ ዲስክ፥ kwami disêkê (hard disk)፤
ዴታ ማጠራቀሚያ ዲስክ። የኮምፕዩተር የውስጥ አካል ሆኖ የሚኖር። ቋሚ የሚለው ቃል የሚያመለክተው፥ ዲስኩ በኮምፕዩተር ውስጥ ኗሪ መሆኑን ለማሳይት ነው። እንደ ፍላፒ ዲስክ የሚመዘዝና የሚከተት እንዲሁም ውጭ የሚቀመጥ አይደለም።
ዲስክ አጠንጣኝ፥ disêkê attänêttañê (disk drive)፤
በዲስክ ላይ ዴታ የሚጽፈውና የሚያነበው ክፍል። ልዩ ልዩ ዲስክ አጠንጣኞች አሉ፤ ለምሳሌ የፍላፒ፥ የዚፕ፥ እንዲሁም የሲዲ ዲስኮች።
ሠንጠረዥ፥ sänêtträzzê (table)፤
በረድፍና ባምድ የተሸነሸነ ጽሑፍ፥ ንባብ፥ ዝርዝር። እያንዳንዱ የሠንጠረዥ ክፍል ሕዋስ ተብሎ ይጠራል። ረድፍ በጐን የተደረደሩትን ሕዋሳት ሲሆን፥ አምድ ደግሞ በቁም የተደረደሩትን ሕዋሳት ያመለክታል። አብዛኛውን ጊዜ ሠንጠረዥ አካባቢ መስመር ይኖረዋል።
ሥነፊደል፥ sênäfidälê (typography)፤
ፊደል ነደፋ። ፊደል ቀረጻ። በፊደል መልክ ብቻ ላይ አያተኩርም። ፊደላቱ በጽሑፍ ላይ የሚኖራቸውን አቀማመጥና አቋቋም ይጨምራል። ዘመናዊ ወይም ድጅታዊ ሥነፊደል ከነባሪው፥ በሂደቱና በውጤት በጣም ይለያል። በሥነፊደል መስክ ውስጥ ያሉ ሰዎች የሥነፊደል አዋቂዎች ተብለው ይጠራሉ።
ሥርዓተ-ነጥብ፥ sêrêatä-nättêbê (punctuation)፤
የንባብ ምልክቶች ። ፥ ፣ ፤ ፦ ፡ ? « » ...
ስሌት፥ sêletê (calculation)፤
ቁጥሮችን ማዳመር፥ ማቃነስ፥ ማባዛት፥ ማካፋልና የተለያዩ የሂሳብ ተግባሮችን መፈጸም።
ንብብ ኤድተር፥ nêbabê edêtärê (text editor)፤
ንባብ መጻፊያ ፕሮግራም። ፕሮግራም አዘጋጆች ኮድ ለመጻፍ የሚጠቀሙበት ፕሮግራም። ንባብ ኤድተሮች ከወርድ-ፕሮሰሰሮች ጋር ሲነጻጸሩ የተለያና የራሳቸው የሆነ ሚና አላቸው፤ ምንም እንኳን በተወሰነ ደረጃ ተመሳሳይት ቢኖራቸውም።
ረድፍ፥ rädêfê (row)፤
በጋድም የተደረደረ፥ የተሰለፈ፥ የተቀመጠ፥ የተነጠፈ። ሠንዘረዥ በረድፍና በዓምድ ይገነባል። በጋድም የተደረደረው የሠንጠረዥ ክፍል ረድፍ ነው።
ሜኒዩ፥ meniyu (menu)፤
መመሪያን፥ ትዕዛዝን ያቀፈ የመስኮት ክፍል።
ንኡስ ሜኒዩ፥ nêusê meniyu (submenu)፤
ባንድ ሜኒዩ ሥር የታቀፉ ቅርንጫፍ ሜኒዩዎች።
ተዘርጊ ሜኒዩ፥ täzärêgi meniyu (pull-down menu)፤
አብይ ሜኒዩ ሲመረጥ ወደታች የሚዘረጋና በዛ አብይ ሜኒዩ ሥር የሚገኙትን የሜኒዩ አባላት የሚያሳይ።
ሜኒዩ ባር፥ meniyu barê (menu bar)፤
አብይ ሜኒዩዎችን በጐን ያቀፈ መስመር። አብዛኛውን ጊዜ ከመስኮት አርእስት ሥር የሚዘረጋ።
ማውስ፥ mawêsê (mouse)፤
ከኪቦርድ ጋር ጎን ለጎን አብሮ የሚሠራ፥ ሁለት ወይም ሦስት መጠቆሚያ ያለው ትንሽ መሣሪያ ነው። የሞኒተርን ገጽ መዳሰስ፥ ፕሮግራሞችን ማስነሳትና ማቆም፥ መስኮቶችን መጎተትና ቦታ መቀየር፥ ሜኒዩ ማስነሳትና መመሪያ መስጠት፥ ገጽን ወደላይና ወደታች ማንሸራተት፥ ማውስን በመጠቀም በየዕለቱ ከምንፈጽማቸው ተግባሮች ጥቂቶቹ ናቸው። የማውስ አብይ ዓላማ፥ ተጠቃሚው ባጭር መንግድ ለፕሮግራሞች መመሪያ እንዲሰጥ ወይም ሥራውን በቅልጥፍና እንዲፈጽም መርዳት ነው። ያለማውስ መሥራት የማንችላቸው ወይም ለመሥራት አጅግ እስቸጋሪ የሆኑ አያሌ ተግባሮች አሉ። ብዙ ፕሮግራሞች የማውስን መኖር ያስገድዳሉ።
ማተሚያ፥ matämiya (printer)፤
ጹሁፎች፥ ሥዕሎችና ሌሎችን ወርቀት ላይ የሚያትም ማሽን። የተለያዩ ማተሚያዎች አሉ። ልዩነታቸው በሚያትሙት የቀለም አይነት፥ ባስታተማቸው እርቅቅና፥ በሚጠቀሙት የቴክኖሎጂ አይነት ላይ ይመሠረታል። ሀገረሰቡ በሰፊው የሚጠቀማቸው ማተሚያዎች ሌዘር፥ ኢንክጀትና ዳትሜትሪክስን ይጨምራል።
መስኮት፥ mäsêkotê (window)፤
በመሠረቱ አንድ መስኮት አራት ማዕዘን ቅርጽ አለው። ከላይ አርእስት፥ ሜኒዩ ባር፥ እንዲሁም ቱልባር፤ ከመካከል የሥራ ቦታ፥ ከታች የሂደት መስመር አለው። በተጨማሪ የሚከተሉት ባህሪዎች አሉት፤ መከፈት፥ መዘጋት፥ ማነስ፥ ማደግ፥ መንሳፈፍና መጥለቅ። የተለያዩ የመስኮት አይነቶች አሉ። ያንዳንዶቹ ቅርጽ ክብ ወይም የተለየ ቅርጽ ነው። ብዙ ሶፍትዌሮች ግልጋሎታቸውን ለተጠቃሚው የሚሰጡት መስኮት በመገንባት ነው። ለምሳሌ፥ ኤለክትሮኒክ መልክት ለመለዋወጥ የምንጠቀማቸው ፕሮግራሞች፥ መልክቶችን ለመጻፍ፥ እንዲሁም ተቀብሎ ለማነበብ የሚያስችሉን በመስኮት ውስጥ ነው።
መረጣ፥ märätta (select)፤
አንድን አካል ማካበብ፥ መለየት፥ ቅድሚያ መስጠት፥ ወይም ለስራ ማዘጋጀት። ለምሳሌ ካንድ ንባብ የተወሰነ ቃል ማውጣት፤ የፋይል ሜኒዩ ማስነሳት፤ ካማራጮች ውስጥ የተወሰኑትን መለየትና የመሳሰሉት ይገኙበታል። ሜኒዩ መረጠ፥ ቃል መረጠ፥ ፎንት መረጠ እንዲሉ።
ልክ፥ lêkê (measurement)፤
ያንድ ነገር መጠን፤ ለምሳሌ ቁመት፥ ስፋት፥ ውፍረት፥ ቅጥነት፥ ርዝመት፥ ክብደት፥ ጥብቀት፥ እንዲሁም የመሳሰለው።
ምስጢር ቃል (ስውር-ቃል)፥ misêttirê (cyphertext)፤
በቁልፍ አማካኝነት ከተነባቢነት ወደ ምስጢርነት የተቀየረ ምስጢር። የተደበቀ ምስጢር።
ስድ ንባብ (ኮምፕዩተር ነክ)፥ misêttirê (plaintext)፤
ያልተበረዘ፥ ያልተቀየጠ ድጅታዊ ንባብ። በቁሙ የሚነበብ። እንደጻፉት የሚኖር፥ የሚታይ፥ የሚታተም።
ተለምዷዊ ምስጢር አደባበቅ፥ tälämêdwawi mêsêttirê adäbabäkê (conventional cryptography)፤
ይህ ሐረግ ከጊዜ ጋር የተያያዘ ነው። ዘመናዊ የምስጢር አደባበቅ ዘይቤዎች ከመውጣታቸው በፊት ዴታዎችን ወደ ምስጢር ቃል የመለወጡ ተግባር የድብቅ ቁልፍ ይጠይቅ ነበር። ሚስጥር ላኪውና ተቀባዩ አንድ የድብቅ ቁልፍ ይኖራቸዋል። ላኪው ከዴታው በዚህ ቁልፍ ሚስጥራዊ-ቃል ከፈጠረ በኋላ ወደ ተቀባዩ ይልካል። ተቀባዩ በተመሳሳይ ቁልፍ ሚስጥራዊ-ቃሉን ይፈተና ተነባቢ ጽሁፍ ያወጣል። ላኪውና ተቀባዩ የሚስጥር ቁልፋቸውን በሚስጥር መጠበቅ አለባቸው። ይህ መንገድ በብዛት ተጠቃሚነትን ያገኘው ባሜሪካ የመንግሥት ድርጅቶች ውስጥ ነው። ቁልፋቸውን ሌላ ሰው ካወቀ ምስጢራቸው ተጋለጠ ማለት ነው። በመሆኑም ምስጢርን በዚህ መንገድ መደበቅ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው።
ድብቅ ቁልፍ፥ dêbêkê kulêfê (private key)፤
ከገሀድ-ቁልፍ ጋር ተዛምዶ የሚሠራ፥ ምስጢር-ቃል መፍቻ።
ገሀድ-ቁልፍ፥ gähädê-kulêfê (public key)፤
ከድብቅ-ቁልፍ ጋር ተዛምዶ የሚሠራ፥ ንባብ ወደ ምስጢር-ቃል መለወጫ።
ድጅታዊ ፊርማ፥ dêjêtawi firêma (digital signature)፤
የሰነድ ደህንነት ማረጋገጫ። የላኪን ማንነት መለያ።
ሃቴማላ፥ hatemala (HTML)፤
ሃቴማላ፥ ሰነዶች በዌብ ገጽ ላይ እንዴት መታየት እንዳለባቸውና መልካቸውስ ምን መምስል እንዳለበት መግለጫ ቋንቋ ነው። የገጹ ስፋት፥ የፊደላት አይነትና ቀለም፥ ያርስቶች አቋቋም፥ ያንቀጾች አቀማመጥ ደንበር፥ የግራፊክስ ምስሎች አሰካክ፥ ካንድ ሰንድ ወደሌላ መስፈንጠሪያ መንገዶችንና የመሳሰሉትን ይገልጻል። ባጭሩ፥ ሃቴማላ የገጽ መግለጫ ቋንቋ ነው።
ሆሄ ፥ ሆሄያት (ለብዙ)፥ hohe/hohiyatê (character)፤
ማንኛውም ተነባቢና አናባቢ ፊደል፥ የንባብ ምልክት፥ ሥርዓተ-ነጥብ፥ ቁጥር፥ ምልክት። ለምሳሌ፦ ሀ፥ ለ፥ ሐ፥ መ ... ፤ 1፥ 2፥ 3፥ ...።
ኅላፍ፥ hêlafê (left margin)፤
ከወረቀት ወይም ከገጽ ግራ ጠርዝ እስከ ጽሑፍ መጣያ ያለው ክፍት ቦታ።
ኆኅት፥ ኆኅያት (ለብዙ)፥ hohêtê/hohêyatê kern
በሁለት ወይም ከዛ በላይ ባሉ ፊደላት መካከል ያለ ክፍት ቦታ። ባንድ ቃል ውስጥ ባሉ ሆሄያት መካከል ያለው ክፍት ቦታ።
መረጃ፥ (ዴታ)፥ märäja (data)፤
ስለተካሄደ ወይም ስለተከናወነ ድርጊት ያልተበረዘ ቃል። ስለቦታ፥ ስለሰው ልጅ፥ ስለጠፈርና የመሳሰሉት ያልተበረዘ ቃል። የአፍሪካ የህዝብ ቁጥር፥ ዓመታዊ የኑሮ ገቢ፥ መልክአ-ምድርና የመሳሰሉት እርግጠኛ መረጃዎች ናቸው። የሰው ልጅ ስም፥ ዕድሜ፥ ቁመት፥ መኖሪያ ቦታና ሌሎችም እንደዚሁ መረጃዎች ናቸው። ባጠቃላይ መረጃ ማለት እውን ቃል ስለቦታ፥ ስለድሪጊት፥ ስለተፈጥሮ፥ ስለሰባዊነት እንዲሁም ሌሎች።
መቃኛ ፕሮግራም፥ mäkaña pêrogêramê (browser)፤
ዌብ ገጽ ማንበቢያ ፕሮግራም።
መነሻ ገጽ፥ mänäsha gäšê (home)፤
ኢንተርነት ላይ ባለዌብ ገጾች መነሻ አድረገው የሚያስቀምጡት ገጽ። ብዙ ጊዜ አንድን የኢንተርነት ገጽ ሲጐበኙ በመጀመሪያ የሚመጣው ገጽ።
መዋቅር፥ mäwaqêrê (structure)፤
1ኛ) ያካል አቋቋም፥ አወቃቀር ከላይ እስከ ታች። 2ኛ) በዲስክ ላይ ወይም በሜሞሪ ውስጥ መረጃዎች ሲሰፍሩ የሚኖራቸው አሠፋፈር፥ አገነባብ። በኮምፕዩተር ሳይንስ ዓለም፥ የይዘቶች አጠነቃቀር በዛፍና በተለያዩ ቅርጾች ይመስላል። የዛፍ አቋቋም፥ ሥርን ፥ ግንድንና፥ ቅርንጫፎችን ይጨምራል። እንደ መሰላል ዛፍን መውጣትና መውረድ ይቻላል። ይዘቶችን በዛፍ አወቃቀር ማጠናቀሩ እጅግ ብዙ ጥቅሞች አሉት።
ሲ++፥ ci (C++)፤
በቢየርን ስተሮቭሰተሩፕ (Bjarne Stroustrup) እአአ 1980 መጀመሪያዎች ላይ የተፈጠረ ፕሮግራም መጻፊያ ቋንቋ ነው። ባለፉት አያሌ ዓመታት፥ ሲ++ ከፍተኛ ተቀባይነትንና ዝናን ያተረፈ ቋንቋ ነው። የዓለም አቀፍ የደንብ ድርጅት የቋንቋው የበላይ ጠባቂ ሲሆን፥ ማንኛውም ሰው ያለምንም ጫናና ክፍያ ቋንቋውን ለተፈለገው ጉዳይ መጠቀም ይችላል።
ሰርቨር፥ särêvêrê (server)፤
በኮምፕዩተር መረብ ውስጥ፥ ለተከታይ ኮምፕዩተሮች ልዩ ልዩ ግልጋሎት ሰጪ ኮምፕዩተር፤ አባወራ ኮምፕዩተር።
ሰነድ-ተቋም-ደንጋጊ (ሰተደ)፥ sänädê-täkwamê-dänêgagi (DTD: Document Type Definition)፤
በኤማላ (XML) አዲስ የምልክት ቋንቋ መፍጠሪያ ፋይል ወይም ክፍል።
ሲ/ኤስ/ኤስ፥ ci/esê/esê (CSS)፤
የዓለም-አቀፍ-ዌብ ኮንሰርሽየም ሥራ ነው። ከሃቴማላ (HTML) ጋር ተዳብሎ የሚሠራ ቴክኖሎጂ ነው። ጽሑፎችን፥ ሥዕሎችን፥ እንዲሁም ሌሎች የዌብ ገጽ ነገሮችን በረቀቀ መንገድ፥ አቀማመጣቸውን እንዲሁም መልካቸውን በገጽ ላይ ለመግለጽና ለመቆጣጠር ይረዳል።
ሶፍትዌር፥ sofêtêwerê (software)፤
ኮምፕዩተር ላይ ሥራዎችን ለማካሄድ የሚያስችሉ ፕሮግራሞች ፤ ካሠራር መመሪያዎች ጋር።
ስክ-ንባብ፥ sêkê-nêbabê (string)፤
ካንድ በላይ ሆሄያት የያዘ። ቃል ወይም ኢቃል፥ ሐረግ ወይም ኢሐርግ፥ ዐርፍተ-ነገር ወይም ኢዐርፍተ-ነገር። ስክ-ንባብ የግድ ቃል፥ ሐረግ ወይም ዐርፍተ-ነገር እንዲሆን አይገደድም። ለምሳሌ፥ ሀሀሀሀ፥ ለለለለ፥ ሐሐሐሐ እና ሀለሐመ ስክ-ንባብ ናቸው።
ኆኅት-ፊደል፥ hohêtê-fidälê (blank space)፤
በቃላት መካከል የሚገባው ክፍት ቦታ። የሁለት ነጥብ እኩሌታ።
መመሪያ-ቃል፥ hohêtê-fidälê (statement)፤
በኮፕዩተር ፕሮግራም ውስጥ፥ እያንዳንዱ ትዕዛዝ ወይም መመሪያ።
ምልክት-ቃል፥ mêlêkêtê-kalê (tag)፤
በኤማላ (XML) ሰነዶች ውስጥ ይዘቶቹን የሚገልጸው ቃል፤ በ(<>) ምልክት የሚታጠረው። ለምሳሌ፥ እንደ <ስም> እና </ስም> ያለው። በሃቴማላ (HTML) ዘንድ ግን፥ ምልክት-ቃል ተነባቢው ነገር እንዴት ዌብ ገጽ ላይ መታየት እንዳለበት ለመቃኛ-ፕሮግራም መመሪያ ይሠጣል። ለምሳሌ፥ <center>አዲስ አበባ</center> «አዲስ አበባ» የሚለው ሐረግ መካከል ላይ እንዲጻፍ ያደርጋል።
ሰያሚ-ቃል፥ säyami-qalê (XML entity)፤
አኅጽሮተ-ቃላትንና ቅጽል ስሞችን ይመሠርታል። ለምሳሌ፥
ዐዋጅ-ቃል፥ awajê-qalê (declaration)፤
በኮምፕዩተር ፕሮግራም ውስጥ ተውላጠ-ቃል (variable) መደንገጊያ/መሰየሚያ። በራም ውስጥ፥ ተውላጠ-ቃላት ልዩ ልዩ ዴታ መጠበቂያ ቦታ ናቸው።
ቃል፥ qalê word
አንድ ወይም ካንድ ፊደል በላይ የያዘ፥ ትርጉም ያለው ስክ-ንባብ።
ኧንግል ብራኬት፥ anêgêlê-bêraketê (angle bracket)፤
የሂሣብ ምልክት «<» እና «>»።
ተመም (ተደጋጋሚ መጠይቅና ምላሽ)፥ tämämê (FAQ Frequently Asked Questions)፤(
ተመም አንዱ የኢንተርነት ባህል ነው። በውይይት መድረኮች ውስጥ ተመሳሳይ ጥያቄዎች በጣም ተደጋግመው ይቀርባሉ። ድግግሞሹን ለመቀነስ አብዘኛውን ጊዜ የሚቀርቡ ጥያቄዎች ከነመልሳቸው ይጠናቀሩና ለተሳታፊዎች ይቀርባሉ። ተሳታፊዎች ጥያቄ ከማቅረባቸው በፊት ያሉትን መጠየቆችና ምላሾች የማንበብ ኃላፊነት ይጠበቅባቸዋል። ይህ ዘይቤ ከመስፋፋቱ የተነሳ፥ በሶፍትዌር ዓለም፥ ድርጅቶች ተመሳሳይ ሰነድ እያዘጋጁ ደንበኞቻቸውን ለመርዳት ይሞክራሉ።
ታብ፥ tabê (tab)፤
ኪቦርድ ላይ የሚገኝ ቁልፍ ነው። ተግባሩ፥ ከርሰርን ከግራ ወደ ቀኝ ወይም በተቃራኒው አቅጣጫ በእኩል በተከፈለ ቦታ ማሸጋገር ነው።
ተውላጠ-ቃል፥ täwêlatä-kalê (variable)፤
ተውላጠ-ቃላት በመሠረቱ ዕሴት መወከያ፥ እንዲሁም ፎርሙላ መግለጫ ቃል ናቸው። ከኮምፑዩተር ፕሮግራም አንፃር፥ ተውላጠ-ቃላት የሚከተሉት ጠባያት አላቸው።
ትልቆቹ/ትንሾቹ ፊደላት፥ têlêqoçu/tênêshoçu fidälatê (Capital/Small letters)፤
በላቲን ሥርዓተ-ፊደል ውስጥ በሁለት መልክ የሚጻፉት ፊደላት። ትልቆቹ ፊደላት (Capital letters) A, B, C,..., Z ሲሆኑ ፥ ትንሾቹ ፊደላት (Small letters) ደግሞ a, b, c, ..., z ናቸው።
ነጠላ ጥቅስ ምልክት፥ näTäla Têkêsê mêlêkêtê (single quote)፤
በላቲን ሥርዓተ-ፊደል፥ የጥቅስ ምልክት «'»።
ስድ ንባብ (ንባብ)፥ sêdê nêbabê (plain text)፤
ተነባቢ ቃላት፥ ዐርፍተ-ነገሮች። ከኮምፕዩተር አንፃር፥ «ስድ ንባብ» ሲባል ቃል ለቃል ድጅታዊ መልክ ያለው፥ ከሌላ ነገር ጋር ያልተዛነቀ፥ ያልተደባለቀ።
አኀጸሮተ-ቃል፥ ahêšärotä-qalê (abbreviation)፤
አንድ ወይም ካንድ በላይ የሆኑ ቃላትን ባጭር ቃል መጥራት። ለምሳሌ፥ አዲስ አባባ ዩንቨርስቲ (አአዩ)፥ አዲስ አበባ (አአ)፥ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር (ኢተማ)፥ ወዘተ።
ዐረፍተ-ነገር፥ aräfêtä-nägärê (sentence)፤
በሰዋሰው ህግ መሠረት ታነጸው፥ ባራት ነጥብ የተቋጠሩ ቃላት።
አንቀጽ፥ anêqäšê (paragraph)፤
ካንድ በላይ ዐረፍተ-ነገሮችን የያዘ የገጽ ጽሑፍ።
አዲስ መስመር፥ adisê mäsêmärê (new line)፤
የአዲስ አንቀጽ (paragraph) መጀመሪያ። ወደሚቀጥለው መስመር።
የፍለጋ ኢንጅን፥ yäfêläga inêjênê (search engine)፤
ኢንተርነት ውስጥ ሰነድ ወይም ገጽ መፈለጊያ የዌብ ገጾች፤ እንደ www.google.com፥ www.altavista.com እና የመሳሰሉት።
ኤማላ ኢለመንት፥ emala ilämänêtê XML element
ኤማላ የይዘት መግለጫ ቋንቋ ነው። እያንዳንዱ የይዘት-መግለጫ ነገር የምልክት
ቃል ተብሎ ይጠቀሳል። ይህ የምልክት ቃል የሚደነገገው የኤማላን ኢለመንት
በመጠቀም ነው።
ቀጣይ-ቃል፥ qäTayê-qalê (hyperlink)፤
የዌብ ገጽ ሰነዶች አስተሳሳሪ፥ አስተባባሪ፤ ከገጽ ወደ ገጽ አሸጋጋሪ። ይህ ቃል <a href="www.senamirmir.org">ስንምርምር ገጽ</a> ወደ ስነምርምር ገጽ መስፈንጠሪያ ነው።
ዓለም አቀፍ ዌብ ኮንሰርሽየም፥ alämê aqäfê webê konêsärêshêyämê (World Wide Web Consortium (W3C))፤
በፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ፥ የዌብን አሠራርና ደንብ በበላይነት የሚመራና የሚቆጣጠር ተቋም። የዓለም አቀፍ ዌብ ኮንሰርሽየም ገጽ http://www.w3.org ነው።
ኤማላ፥ emala (XML);
የExtensible Markup Language አኅጽሮተ-ቃል። በተለምዶ XML የሚለው አኅጽሮተ-ቃል ባማርኛ ኤከስ/ኤም/ኤል ይሆናል። ይህን የመጨረሻ ቃል እንዲያጥር ቢደረግ ኤ/ክስምል ይመጣል። ሌላው አማራጭ ለራሱ ለExtensible Markup Language እኩሌታ ያማርኛ ትርጉም ማበጀት ነው። ተስፋፊ አካላይ ቋንቋ፤ ተስፋፊ አመላካች ቋንቋ፤ ወይም የተስፋፊ መቀነፊያ ቋንቋ፤ ለሙከራ ያህል ጥሩ ናቸው። በአኅጽሮተ-ቃል መልካቸው በተራ፦ ተ/አ/ቋ እና ተ/መ/ቋ ይመጣሉ። ስየማ ውስጥ አሁኑኑ ከመግባት፥ በኤማላ መርጋቱ ለጊዜው ያመቻል።
ዓምድ፥ amêdê (colmn);
ገጽ ላይ በቁም የተሸነሸነው ንባብ። በቁም የተሸነሸነው የሠንጠረዥ አካል።
ዕሴት፥ êsetê (value)፤
ቁጥር፥ ሆሄ፥ ቃል፥ ንባብ፥ ወዘተ፤ የሚመጠን፥ የሚቆጠር፥ የሚተመን።
ገጽታ፥ gäšêta (screen)፤
ጹሑፎች፥ ግራፊክሶችና የመሳሰሉት የሚታዩበት የኮምፕዩተር ሞኒተር ክፍል፤ ፊት ለፊት ያለው።
ኮምፕዩተር መረብ፥ komêpêyutärê märäbê (computer network)፤
በሽቦ፥ በስልክ፥ በሳተላይት እንዲሁም በልዩ ልዩ መንገድ ተሳስረው የሚሠሩ ኮምፕዩተሮች።
ዌብ ገጽ፥ webê gäšê (web page)፤
ተቋሞች፥ ድርጅትቶች፥ ግለሰቦች፥ ኢንተርነት ላይ የሚያወጧቸው ጹሑፎች፥ ሰነዶች፥ ድምጾችና የመሳሰሉት።
ዴታ አይነት፥ deta ayênätê (data type)፤
የቁጥር አይነቶች፦ ሙሉ ቁጥር (integer)፥ ፍሎት ቁጥር (float)፤ ሆሄ (character)፥ ቡሌን፥ እውነት (true)፥ ሐሰት (false)። ቁጥሮች በመጠን ማለትም በሚይዙት የሜሞሪ ስፋትና ጥበት ይከፈላሉ፥ ለምሳሌ፦ byte፥ short፥ int፥ long፥ float፥ double እና የመሳሰሉት።
ድርብ የጥቅስ ምልክት፥ dêrêbê yäTêqêsê mêlêkêtê (double quote)፤
በላቲን ሥርዓተ-ፊደል ድርብ የጥቅስ ምልክት «"»።
ኤመልክት መድረክ፥ emälêkêtê mädêräkê (mailing-list group)፤
በኤለክትሮኒክ መልክት ልውውጥ ላይ የተመሠረተ፥ የመወያያ ስብስብ። አባላቱ መልክቶችን በመላላክ የሚነጋገሩበት፥ የሚለዋወጡበት፥ የሚማሩበት።
ዩንኮድ፥ yunêkodê (Unicode)፤
1ኛ) ፊደላትን ኮምፕዩተር ውስጥ ለማስገባት ወይም በመስመር ለመለዋወጥ፥ ፊደላቱ የማያሻማ ኮድ መሰየም አለባቸው። ኮምፕዩተሮች ፊደላቱን የሚለዩት በዛ ኮድ እንጂ በመልካቸው አይደለም። ኮዶቹ የሚሠሩት ከቁጥር ነው። አያሌ የኮድ ስልቶች በሥራ ላይ ውለዋል። በዚህ የተነሳ አለመግባባት፥ አለመጣጣም፥ ግጭት አለ። ዩኒኮድ አንድ ወጥ የሆነ ስልት ወይም ሠንጠረዥ ለመገንባት የሚሞክር መደበኛ ወይም ስታንዳርድ (standard) ነው። 2ኛ) ዩኒኮድ መደበኛ (Unicode standard)፦ ለኮምፕዩተሮች ሥራ፥ የዓለም ቋንቋዎች ፊደላትን በኮድ የሚወክል ሠንጠረዥ፤ መደበኛ። 3ኛ ዩኒኮድ ኮንሰርሽየም (Unicode consortium)፦ በፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ፥ ፊደላትን ኮድ የሚሰይም ዓለም-አቀፋዊ (ዓለማቀፋዊ) ተቋም ነው። በዩኒኮድ መሠረት እያንዳንዱ ፊደል ሁለት ባይን የሜሞሪ ቦታ ይይዛል።
ይዘት፥ yêzätê content
ያንድ ነገር መሠረታዊ አካል። ፋይሎች ውስጥ የተቀመጠ ጹሑፍ፥ መረጃ፥ ድጅታዊ-ሥዕል፥ ድምፅ፥ ወዘተ።
የጥቅስ ምልከት፥ yäTêqêsê mêlêkêtê (quotation mark)፤
የኢትዮጵያ ፊደል የጥቅስ ምልከት (፟፠)።
ግልየት፥ gêlêyätê (right margin)፤
ከቀኝ ጠርዝ እስከ ጽሑፍ መወደቂያ ያለው ክፍት ቦታ።
ዴታቤዝ፥ detabezê (database)፤
በኮምፕዩተር ማዕከላዊ መረጃ/ዴታ ማከማቻና ማስተዳደሪያ ስልት።
ድንጋጌ፥ dênêgage (definition)፤
ያንድ ነገር ምንናማንነት ገለጻ። ለምሳሌ፥ የቃላት ትርጉም፤ ይህ ምዕላደ-ቃላት ሊያደርግ እንደሚሞክረው።
ጃቫ፥ java (Java)፤
በሰን ማይክሮሲሰትምስ (Sun Microsystems) የተፈጠረ ፕሮግራም መጻፊያ ቋንቋ። ባሁኑ ሰዓት ከፍተኛ ተወዳጅነት ያተረፈ። ፕሮግራም ለመጻፍ አመቺ የሆነ።
ገጽ መግለጫ ቋንቋ፥ gäšê mägêläça qwanêqwa (page description language)፤
የጹሑፎች እንዲሁም የሥዕሎች አቀማመጥ መወሰኛ ቋንቋ፥ እንደ ሃቴማላ ያለው።
ግርጌ ማስታወሻ፥ gêrêge mašêtawäsha (footnote)፤
የገጾች የታችኛው ቦዶ ክፍል ኀዳግ ተብሎ ይጠራል። በዚህ ሥፍራ ገጹ ውስጥ ያለውን ጽሑፍ ለመደገፍ የሚጻፍ ማብራሪያ፥ ጥቅስ፥ ማስረጃ፥ አጣቃሽ ነገር ግርጌ ማስታወሻ ይባላል።
አባሪ ለኤማላ ኢለመንት፥ abari läemala ilämänêtê (XML attribute)፤
የኤማላን ኢለመንት ድንጋጌ የሚያስፋፋ።
ፊደል፥ fidälê (alphabet)፤
ከሀ--ፐ፥ ከ0-9፥ የመሳሰለው።
ፋይል፥ fayêlê (file)፤
የተጠናቀረ ወይም የተደራጀ ድጅታዊ ይዘት። ማንኛውም ፋይል እነዚህን
ጠባዮች ይጨምራል፦ ስም፥ ጊዜ፥ መጠንና አይነት።
ፎንት፥ fonêtê (font)፤
ፊደል፥ አኀዝ ፥ ሥርዓተ-ነጠብ፥ አይነተኛ ምልክቶችን ያቀፈ፤ አንድ አይነት መልክ፥ መጠን፥ ቀለም ያለው፤ ጹሑፎችን የሞኒተር ገጽታ ላይ ለማሳያት ወይም ወረቀት ላይ ለማተም የሚያስችል፤ በፎንት ቋንቋ የተቀረጸ።
ፕሮግራም፥ pêrogêramê (program)፤
ፕሮግራም ስንል፥ የኮምፕዩተር ፕሮግራም ለማለት ነው። ልዩ ልዩ ተገባራት ማለትም ጹሑፎችን፥ ዴታቤዞችን፥ ሥዕሎችን፥ ስፕርድሽቶችንና ሌሎች ሥራዎችን ኮምፕዩተር ላይ ለማከናወን የሚያስችለን። ፕሮግራሞች በልዩ ልዩ ቋንቋ ይጻፋሉ። ለምሳሌ፥ ሲ (C)፥ ሲ++ (C++)፥ ጃቫ (Java) እና የመሳሰሉት።
ፕሮግራም መጻፊያ ቋንቋ፥ pêrogêramê mäšafiya qwanêqwa (programming language)፤
ለኮምፕዩተሮች መመሪያ ወይም ፕሮግራም መጻፊያ ቋንቋዎች፤ ጃቫ (Java)፥ ሲ (C)፥ ሲ++ (C++) እንዲሉ።
ፓርሰር፥ parêsärê (parser)፤
ፓርሰሮች በመሠረቱ ያንድን ሰነድ ይዘት በተጠየቀው መንገድ ማሰስና ውጤቱን ማቅረብ ይችላሉ። የኤማላ ፓርሰሮች (parsers) የኤማላን ሰነድ ተንትነው በተፈለገው መንገድ መሠረት ውጤታቸውን ያቀርባሉ።
ፕሮግራም ጸሐፊ፥ pêrogêramê šähäfi (program writer)፤
የፕሮግራም ቋንቋዎችን ተጠቅሞ ፕሮግራም የሚጽፍ፤ ሞያው ያደረገ። |
|
contact@senamirmir.org |