XML Overview in Amharic
|
|
ኤማላ (XML)
፟ኤማላ፠ (Extensible Markup Language) ፥ ከዕለት ወደ ዕለት ፥ የኢንተርነትን መልክአ-ምድር አየቀየረ ነው። እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ እንደማይሄድ ጉልህ ምልክቶች አሉ። ስለዚህ ለኤማላ ልባዊ ትኩረት ልንሰጥ ይገባ ይሆናል። በዚህ ክፍል ስለኤማላ ባጭሩ አብይ ነጥቦችን እናወሳለን ፦ የኤማላና ሃቴማላ ግንኙነት ፥ ኤማላ ሰነድ ፥ ሰነድ አይነት ደንጋጊ ፋይል ፥ ኤማላ ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች ስላለው ድጋፍና የመሳሰሉት። ኤማላና ሃቴማላ
ኤማላ ምሳሌአሁን የኤማላ ሰነድ ምን እንደሚመስል በተግባር ለማየት እንሞክራለን። ባለፈው ክፍል የተጠቀምነውን ምሳሌ እዚህ በማምጣት ፥ ወደ ኤማላ-ሰነድ እንቀይረዋለን።
ከሁለቱ የመጀመሪያ መስመሮች ፦ አንደኛው የሰነዱን አይነት ሲያበስር ሁለተኛው ደግሞ ክዳኖቹ የተሰየሙበትን ፋይል ስም። ከመጀመሪያ ሁለት መስመሮች ውጭ የተጠቀምናቸው ቃለ-ምልክቶች በሙሉ ፟ባለሰነድ-ሠራሽ፠ ናቸው። ሥየማቸውና ያሰካክ መዋቅራቸው ፥ ስሙ ፟rivers.dtd፠ በተባለው ፋይል ውስጥ ይገኛል። ስማቸውን መፍጠር ፥ መቀየር ፥ ርባታቸውን መቀነስ ወይም መጨመር ፥ እንዲሁም መዋቅራቸውን መለወጥ እንችላለን። ለዚህ ነው ፥ ቃለ-ምልክቶችን ባለሰነድ-ሠራሽ የምንላቸው። ወሰን የሌለው ኃይል ያጐናጽፉናልና። የቃለ-ምልክቶቹ አሰካክ ፥ ሥርዓትና ቅደም ተከተል ስላለው ፥ በጥንቃቄ ያን ማክበር ግዴታ ነው። በምሳሌያችን ፥ የ<rivers>> ቃለ-ምልክት በውስጡ የ<river> ቃለ-ምልክት ያቅፋል። የ<river> ቃለ-ምልክት ደግሞ በተራው የ<name> እና <length> ያዝላል። ይዘት ለማቀፍ የሚፈቀድላቸው ቃለ-ምልክቶች <name> እና <length> ናቸው። የተሰየሙት ሥራ ያ ስለሆነ። ይኸን ያሰካክ ሥርዓት ብናዛባ ፥ ሰነዳችን የተሟላ አይሆንም። ሳናውቅ ስህተት ብንሠራም ፥ ሰነዱ እንደጐደሎ ይቆጠራል። እያንዳንዱ ከፋች ቃለ-ምልክት በወገኑ የግድ መገጠም አለበት። ለምሳሌ <rivers> በ</rivers> ቃለ-ምልክት። የሌሎቹም እንደዚሁ። ግድፈት ያዘሉ ቃለ-ምልክቶች ፥ ሰነድን ለጥፋት ያበቃሉ። ቃለ-ምልክቶቹ ፥ በሰነድ-አይነት-ደንጋጊው ፋይል ውስጥ ወይም እዚህ በቅድሚያ የተሠየሙ መሆን አለባቸው። በደፈና አነጋገር ፥ ላፈጣጠራቸው ፥ ላጠቃቀማቸው ፥ እንዲሁም ላተረጓጐማቸው ሙሉ ኃላፊ እኛ ነን። ምንም እንኳን እዚህ ባንነጋገርበትም ፥ የrivers.dtd ፋይል ይዘት እንደሚከተለው ነው።
ቢያንስ አንድ የኤማላ ፟ሥራ-በቅ፠ (Application) ፥ አንድ ወይም የተሳሰሩ ካንድ በላይ ሰነድ-አይነት-ደንጋጊዎች ፥ እንዲሁም አንድ ወይም የተሳሰሩ ካንድ በላይ ኤማላ ሰነዶች ያዝላል። ኤማላና የኢትዮጵያ ቋንቋዎችእንበል ፥ በራሳችን ቋንቋ የኤማላ ሰነድ ማዘጋጀት እንፈልጋለን! የሰነዳችን ይዘት ባማርኛ ከተጻፈ ፥ ሁሉንም አማርኛ ባማርኛ ብናደርገው ላዘጋጁም እንዲሁም ለተጠቃሚው ያመቻል። ስለዚህ ፥ ያማርኛ ኤማላ ሰነድ እነሆ፦
ይህ ምሳሌ ፥ ከቋንቋ በስተቀር ፥ በሁለመናው ከዚህ በፊት ካያነው አይለይም። በግል ቋንቋ ሲጻፍ ፥ ለማንበብና ላጠቃቀም ይቀላል። ዓላማችን መፍትሄ መሻት ነውና። ሥራችን የተሟላ እንዲሆን ፥ ሰነድ-አይነት-ደንጋጊ ፋይሉን እናሻሽል።
እንደኛ ከሆነ ፥ ሥራችንን በዚህ ደረጃ አጠናቀናል። ሰነዳችን ሥራ-ብቁ ነው። ይሁን እንጂ ፥ ምንም እንኳን ፥ ይህ ሥራችን በጐ መስሎ ቢታይም ፥ ለኤማላ 1.0 ከፍተኛ ስህተት አለው። ኤማላ 1.0 በኢትዮጵያ ፊደል የተጻፉ ቃለ-ምልክቶች ማለትም አብይ-አንቀጾች ፥ ጠባየ-አንቀጾች ፥ እንዲሁም ሰያሚ-አንቀጾች በጭራሽ አይቀበልም። ስለሆነም ፥ ይህ ሰነድ ተቀባይነት ያጣል። ለሥራ ብቃት የለህም ይባላል። ርባነቢስ እንዲሉ። አጥብቀን ማስተዋል ያለብን ነገር ቢኖር ፥ የይዘቱ ባማርኛ መጻፍ የችግሩ መንስኤ አለመሆኑን ነው። በዚህ ጉዳይ ፥ የኤማላ ጠብ ከይዘቱ ጋር አይደለም ፥ ከቃለ-ምልክቶቹ ፊደል እንጂ። በመዋቅር ረገድ ግን የተጣሰ ሕግ የለም። ለመሆኑ ፥ ኤማላ 1.0 ለምን የኢትዮጵያን ፊደል አይቀበልም? መልሱ ከዩኒኮድ ታሪክ ጋር ይያያዛል። ኤማላ ቁጥር 1.0 የወጣው እአአ 1998 ነበረ። በጊዜው የነበረውን የዩኒኮድ ደንብ ቁጥር 2.0 በማያሻማ መንገድ ደገፈ። ከዛ በኋላ ፥ ዩኒኮድ 3.0 ሲወጣ ፥ የኢትዮጵያ ፊደልና ጥቂት ሌሎች ተቀባይነት አግኝተው ታተሙ። ኤማላ ግን ከዚህ አዲስ ሁኔታ ጋር ራሱን ስላለቀራረበ ፥ በዩኒኮድ 3.0 እና ከዛ በኋላ የወጡትን ፊደላት ሳይቀበል እንዳለ አለ። በመሆኑም ፥ በኤማላ 1.0 ላይ የሚመኩ ፕሮግራሞች (XML applications) ፟ከዩኒኮድ 2.0፠ ውጭ በሆኑ ፊደላት የተጻፉ ቃለ-ምልክቶችን አንቀበልም ይላሉ። በይዘት ደረጃ ግን ችግር የለባቸውም። ቃለ-ምልክቻቸው ወይም መዋቅራቸው ተቀባይነት ያጡ ሰነዶች ፥ ሥነ ሥርዓት የጐደላቸው ሰነዶች ይሆናሉ። ጭላንጭላዊ መፍትሄበቅርቡ ይህንና የመሳሰሉትን ችግሮች ለማስወገድ የቀረበ ውጥን አለ። ስሙ ፟ሰማያዊ እንጆሪ፠ (Blueberry) የተሰኘው ውጥን ፥ በዩኒኮድ 3.0 እና 3.1 የወጡትን ፊደላት በኤማላ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ይጠይቃል። ጉዳዩ ለውይይት ተከፍቶ ፥ ሃሳብ እየተሰነዘረበት ነው። ማንኛውም ሰው ፥ ሃሳብ የመስጠት መብቱ ሙሉ በሙሉ የተጠበቀ ስለሆነ ፥ አግባባዊ አስተያየት መሰንዘር ይበጃል። ውጥኑ በቂ ደጋፍ ካገኘ የማለፍ እድሉ ይጨምራል ፥ ካልሆነ የመውደቅ ዕጣ ይገጥመዋል። ስለዚህ ፥ ምን ማድረግ አለብን?
ምንጮች |
|
smirmir@senamirmir.org ©Senamirmir Project, 2001 |